በዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቮሶግሉ ጋር ተወያየ።
ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቮሶግሉ ጋር በነበራቸው ቆይታም በወቅታዊ የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል።
ውይይቱን አስመልክቶ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በትዊተር ገፃቸው ፥ “የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልዩ መልዕክተኛ እና በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል” ብለዋል።
በውይይታቸውም በመሪዎች ደረጃ በሁለቱም ሀገራት መካከል የሚደረጉ ጉብኝቶችን ማሳደግ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረጉ ምክክሮችን በማሳደግ ዙሪያ መምከራቸውንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል በሁሉም መስክ ያለውን አጋርነት በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያለውን ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።