በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ በተከሰተው ሁከትና ግርግር የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ሰሞኑን በተከሰተው ሁከትና ግርግር አጥፊዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
በባሌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ተስፋዬ ከበደ እንደገለጹት÷ በወረዳው ለጥፋት የተንቀሳቀሰው ቡድን ሲገለገልባቸው የነበሩ የጦር መሣሪያዎች ተይዘዋል።
ከነዚህም ዘጠኝ ሽጉጦች፣ አራት ክላሽንኮቭ ጠብ መንጃዎች እና በቁጥር 434 የሚሆኑ ተቀጣጣይ የፈንጂ ገመዶች ይገኙበታል፡፡
በተከሰተው ሁከትና ግርግር በወረዳው ኅብረተሰቡ ሲገለገልባቸው የነበሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በወረዳው የ64 አባወራ መኖሪያ ቤቶች ሲወድሙ በዚህም ከ1ሺህ 200 በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ኮማንደሩ አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያና ኅብረተሰቡ በሚገለገልበት ድልድይ ላይ ተጠምዶ የነበረ ተቀጣጣይ ፈንጂ የጸጥታ ኃይሎች ማክሸፋቸውን አስረድተዋል፡፡
በወረዳው በሁከት ፈጣሪዎች በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ የነፍስ ማጥፋት፣ ዘረፋና የቤትና የንብረት ቃጠሎ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተዘረፉ 101 የሚሆኑ የጦር መሣሪያዎች፣ ከመሥሪያ ቤቶቹ የተዘረፈ ንብረት እና ከአርሶ አደር የተዘረፉ 85 የቀንድ ከብቶችም መመለሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡