Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ በላቅ ትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና በማረጋገጥ በላቅ ትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ‘የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና’ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ዓውደ-ርዕይ ከፍተዋል፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ÷ ብልጽግና ፓርቲ በሀሳብ ልዕልና በማመን ሀሳብ ይዞ፣ በሀሳብ ልእልና ታግሎ፣ በሀሳብ ልዕልና በህዝብ ተመርጦ ከህዝባችን ጋር ዝቅ ብሎ በመስራት ላይ የሚገኝ የህዝብ ፓርቲ መሆኑን በእነዚህ አምስት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች የሚመሰክሩና የፓርቲውን ማንነትና ዓላማ በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አበባ እናደርጋታለን ብለን ከተማችንን ጽዱ፣ ውብና ለኑሮ ተስማሚ፣ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል በማድረግ ቃላችንን በተግባር በመፈጸም እንዲሁም ለሰው ልጆች ቅድሚያ በመስጠት በልማት ስራዎች የነዋሪውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሰው ተኮር ስራዎችን ሰርተን የበርካቶችን እምባ አብሰናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ባጋጠሙን ፈተናዎች ከጎናችን ያጣናቸውና በመንገድ የቀሩም ነበሩ ያሉት ከንቲባዋ ÷ ሆኖም ግን ፓርቲያችን አሁንም በፅናትና በድል ወደፊት ቀጥሏል ብለዋል፡፡

ቃላችንን አድሰን፣ ተግዳሮቶችን አስወግደንና እጅ ለእጅ ተያይዘን በጀመርነው መንገድ ህዝባችንን ዝቅ ብለን የምናገለግልበት እንዲሁም የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና በማረጋገጥ በላቅ ትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለንም ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.