የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ ኮቪድ-19 ጫና ቢያሳድርበትም ተወዳዳሪነቱና ተፈላጊነቱ እንደቀጠለ ነው–ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12 ፣ 2012 ( ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ ኮቪድ-19 ጫና ቢያሳድርበትም፤ ተወዳዳሪነቱና ተፈላጊነቱን ማስቀጠሉን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ አስታወቁ።
በመናኽሪያዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ኮቪድ-19 መከላከያ ተግባራት ይጠናከራሉም ብለዋል ።
ሚኒስትሯ ዘርፉ የኮሮና ወረርሽኝ ጫናና ተጋላጭነት ቢያሳድርበትም፣ተወዳዳሪነቱና ተፈላጊነቱን ግን ጨምሯልም ነው ያሉት ።
በተለይም ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመቀናጀት ወረርሽኙ በዘርፉ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመቀነስ ውጤት እንደተገኘበት ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ከ100 ሺህ በረራዎች የአውሮፕላን አደጋ ተቀባይነት ያለው 0 ነጥብ 4 ነጥብ በማምጣት መቶ በመቶ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ወይዘሮ ዳግማዊት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መስፈርትም በኦዲት ሥራ 91 ነጥብ 7 በመቶ በማስመዝገብ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም 20ኛ ደረጃን ማግኘቱንም አስታውቀዋል።
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተቀመጡትን የሥራ አመራር ሥርዓት የጥራት መስፈርት በማሟላት ዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ISO 90001.2015) ማግኘቱንም አብራርተዋል።
በመናኽሪያዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ወረርሽኙን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት እንደሚጠናከሩም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
ከተግባራቱ መካከልም የመንገደኞችን ሙቀት መጠን መለካትና የእጅ ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ይገኝበታል ብለዋል።
ከዚያም ባለፈ በመናኸሪያዎች የሚሰጠውን አገልግሎት ብዛት በመጨመር፣የተሳፋሪዎችን ቁጥር በግማሽ መቀነስና ርቀትን ማስጠበቅም ሌሎቹ ተግባራት መሆናቸውን አስረድተዋል።
በጉዞ ወቅት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማስጠቀም ሥራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የወረርሽኙ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መጀመሩን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
መከላከልን መሠረት ያደረገና ተከታታይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ከታዋቂ ግለሰቦችና ከበጎ ፈቃደኞች ጋር እየተከናወኑ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።