በለንደን ደርቢ ዌስትሃም ዩናይትድ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት መርሐ ግብሮች ዛሬ ሲካሄዱ በለንደን ደርቢ ዌስትሃም ዩናይትድ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ መድፈኞቹ ወደ ለንደን ስታዲየም በማቅናት ዌስታም ዩናይትድን ይገጥማሉ፡፡
በአርሰናል በኩል ብራዚላዊው ተከላካይ ጋብረኤል ማጋሌሽ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ ጠቁመዋል፡፡
በዌስትሃም ዩናይትድ በኩል ኤድሰን አልቫሬዝ ከቅጣት በኋላ በዛሬው ጨዋታ የሚሰለፍ ሲሆን ÷ጋናዊው ኮከብ ሞሃመድ ኩዱስ የአምስት ጨዋታ ቅጣቱን ባለመጨረሱ በጫዋታው የማይሳተፍ ይሆናል፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ብሬንትፎርድ ከሌስተር ሲቲ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ሆላናዳዊው አሰልጣኝ ሩድ ቫን ኒስትሮይ የሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ በመሆን የመጀመሪያ ፍልሚያውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ 12 ሰዓት ክሪስታል ፓላስ ከኒውካስል ዩናይትድ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከኢፕስዊች ታውን እንዲሁም ዎልቭስ ከቦርንሞውዝ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
ሊጉን ሊቨርፑል በ31 ነጥብ ሲመራ፣ ትላንት ከሳውዝአምፕተን ጋር ተጫውቶ 1 አቻ የተለያየው ብራይተን በ23 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ማንቼስተር ሲቲ በእኩል ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡