Fana: At a Speed of Life!

በይዘቶቻችን ሀገርና ትውልድን ለመገንባት በትኩረት እንሰራለን – አቶ አድማሱ ዳምጠው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በይዘቶቻችን ሀገርና ትውልድን ለመገንባት በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ገለጹ።

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማብሰሪያ እና ስራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በግራንድ ኤሊያና ሆቴል እየተካሄደ ነው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የሚዲያው አመራሮች የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ተባባሪ አዘጋጆች፣ የሚዲያው አጋሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ አድማሱ ዳምጠው በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ አመራሮችና ሰራተኞች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ተመሳሳይ ዓላማ ይዘው የተቋቋሙት የሚዲያ ተቋማት ውህደት አንድ ግዙፍ እና ተደራሽ ሚዲያ ለመመስረት ያለመ ነው መሆኑን ገልጸው፤ በይዘቶቻችን ሀገርና ትውልድን ለመገንባት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ከመጣንበት ይልቅ ገና የምንጓዝበት ጊዜ ረጅም መሆኑን አውቀን የተሻለ ለመስራት የምንዘጋጅበት ነው ያሉት አቶ አድማሱ፤ ሁለቱ የሚዲያ ተቋማት ተዋህደው መሪና ተወዳዳሪ የሚሆን ሚዲያ ፈጥረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በከፍተኛ ሞራል እና የሀላፊነት ስሜት ለትውልድ ግንባታ ኢትዮጵያን እናበስራለን በማለት ገልጸው፤ የህዝብ አብሮነትን መስበክና ለሀገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ዕድገት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ለሀገራችን ግድ የሚለን ባለሙያዎች ሆነን የጋራ መልኮቻችንን የምናፀና መሆን ይኖርብናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነፃ ሀሳቦች የሚሰበኩበትና የሚንፀባረቁበት ሚዲያ እንደሚሆንም አረጋግጠው፤ ሚዲያው አካታችነት እና ተደራሽ ነው ብለዋል።

ይህንን ለማሳካትና ዕውን ለማድረግም የሚመለከታቸው አካላት ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬት ጋር በአብሮነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በመላኩ ገድፍ እና ፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.