1 ሺህ 155 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ መቀጠሉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በዚህ መሰረትም ከሕዳር 4 እስከ ሕዳር 27 ቀን 2017 ድረስ 1 ሺህ 155 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተጠቁሟል፡፡
ተመላሾቹ 446 ወንዶች፣ 631 ሴቶች እና 78 ጨቅላ ህፃናት ሲሆኑ÷ ከእነዚህ መካከልም 218 ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ለተመላሽ ዜጎች ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ የማድረግና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው ከሳዑዲ ዓረቢያ ዜጎችን የመመለስ ሥራ እስካሁን ከ87 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ መመለስ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡