Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ ንግድ ተሰማርተው የተገኙ ላኪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 14 ፣ 2012  (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለወጪ ንግድ የሚውሉ የግብርና ምርቶችን በህገ-ወጥ መንገድ የላኩ እና በክምችት የያዙ ከ59 በላይ ላኪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግብይት የሚፈጸምባቸው የሰሊጥ፣ የነጭ ቦሎቄ፣ የአኩሪ አተር እና የማሾ ምርቶችን ከዓለም አቀፍ ዋጋ በላይ ከምርት ገበያ በመግዛት የግብይት መዛባትን ያስከተሉ ላኪዎች ላይ  እርምጃው መወሰዱ ተገልጿል።

በዚህም ከምርት ገበያ ግብይት መታገድ እስከ ንግድ ፈቃድ እገዳ የሚደርስ እርምጃ መውሰዱን የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባደር ምስጋኑ አርጋ ተናግረዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከክልል መንግስታት የግብይት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀትና የመስክ ኢንተለጀንስ ስራዎችን በማከናወን ምርቶችን በህገ-ወጥ መንገድ በክምችት የያዙ የግብይት ተዋንያን ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው  ጠቁመዋል።

በዚህም በክምችት የተያዙ ምርቶች ወደ ምርት ገበያ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን ይህንን ተግባራዊ ያላደረጉ እና 5 ሺህ 542 ቶን ቀይ ቦሎቄ የሰወሩ 10 ላኪዎች የንግድ ፈቃዳቸው ተሰርዟል፡፡

በተጨማሪም የወጪ ንግድ ምርቶችን የግብይት ስርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር የላኩ 59 ላኪዎች የንግድ ፈቃዳቸው ለሦስት ወራት እንዲታገድ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት ከክልል መንግስታት የግብይትና በወጪ ንግድ ላይ ከሚሰሩ ቢሮዎች፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከግብይት ተዋንያን ማህበራት ጋር በሰራቸው ቋሚ ቅንጅታዊ ስራዎች 374  ሺህ 514 ቶን የሰሊጥ፣ የነጭ ቦሎቄ፣ የቀይ ቦሎቄ፣ የአኩሪ አተር እና የማሾ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገቡ መደረጉን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር  ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.