Fana: At a Speed of Life!

በሀረማያ ከተማ ህገ ወጥ የሞባይል ሲም ካርዶችና መድሃኒቶች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 14 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ሐረማያ ከተማ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ5 ሺህ በላይ ህገ ወጥ የሞባይል ሲም ካርድ ፣ መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶች መያዙን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ ።

የዞኑ  ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ተጠባባቂ ኃላፊ ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ ÷ህገ ወጥ ቁሳቁሶቹ ሐምሌ 12 ቀን 2012 ዓ.ም የተያዙት በሐረማያ ከተማ 02 ቀበሌ በተለምዶ ፍልስጤም ተብሎ በሚጠራው ሰፈር  መሆኑን ገልጸዋል ።

ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው የተቀናጀ ብርበራ ከአንድ ተከራይ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ከ5 ሺህ በላይ የተከፈተና ያልተከፈተ የሞባይል ሲም ካርድ ተይዟል ።

እንዲሁም የተለያዩ ህገ ወጥ መድሃኒቶች ፣ ላፕቶፖች ፣ ዲጂታል ካሜራዎች ፣ ቤንዚን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች በብርበራው ወቅት ተይዟል ።

ተጠርጣሪው ተከራይና የቤት አከራዮቹ ለጊዜው መሰወራቸውን ኢንስፔክተሩ ገልፀው÷ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በፊትም ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ህገ ወጥ የሞባይል ሲም ካርድ በዞኑ ባቢሌ ከተማ ከአንድ ግለሰብ ቤት መያዙን  አስታውሰው ÷ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ሒደት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።

በኢትዮ ቴሌኮም የማእከላዊ ምስራቅ ሪጅን ኦፕሬሽናል ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ሰይድ ÷ ድርጊቱ በአገር ፣ በህዝብና በድርጅቱ ላይ ጉዳትና ኪሳራ የሚያስከትል ተግባር በመሆኑ ህገ ወጥ የሲም ካርድ ዝውውር ወንጀልን ለመቆጣጠር ከፖሊስና ከህብረተሰቡ ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በሀረማያ ከተማ የተያዘው ህገ ወጥ ሲም ካርድ ከየትኛው የሽያጭ ማእከል እንደወጣ ማወቅ ስለሚቻል አስፈላጊውን መረጃ በማጣራት ለፖሊስ እንዲደርስ እናደርጋለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.