Fana: At a Speed of Life!

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች አረንጓዴ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸውን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በዓለም አቀፍ አረንጓዴ የምስክር ወረቀት እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡

የመግባባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) እና የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) ናቸው፡፡

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ስራን ከግምት ውስጥ ያስገባ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የአረንጓዴ አፈጻጸም ተግባራትን በኢኮ-ኢንዱስትሪያል ፓርክ ፅንሰ ሃሳብ መሠረት የአረንጓዴ ምስክር ወረቀት ውስጥ መግባታቸው ለስራ ምቹ እና ተመራጭ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ በአካባቢ ጥበቃ ሕጎች መሰረት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ ያሉበትን ደረጃ በመመዘን ያሟሉትን እውቅና ለመስጠትና ክፍተት ያለባቸው ደረጃውን እንዲያሟሉ ለማድረግ ስምምነቱ ይረዳል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ በኃይል እና በውኃ አጠቃቀም እንዲሁም በተረፈ ምርት አወጋገድና ቅነሳ በሁሉም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የተሰሩትን ስራዎች በመመዘን እውቅና ለመስጠት ያለመ ነው መባሉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም አራት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በመመዘን እውቅና የመስጠት ሥራ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.