Fana: At a Speed of Life!

የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር ጀርመን ድጋፍና ትብብር እንደምታደርግ ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር የጀርመን መንግስት በትብብር እንደሚሰራና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የውጭ ፖሊሲ አምባሳደር ጌሳ ብራቲጋም እና በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ጆን ሄንፊልድ ጋር በትብብረ መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ በሴቶች መብት እንዲሁም ሴቶች በሰላምና ደህንነት፣ በብሔራዊ ምክክር እና በሽግግር ፍትህ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሥራ ሃላፊዎቹ በስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ ሴቶችንና ወጣቶችን በማብቃት እንዲሁም የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን በማጠናከር ዙሪያም መምከራቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ ኤርጎጌ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያ ሴቶች በሀገራዊ ምክክርና በሽግግር ፍትህ ሂደት ውስጥ ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲሁም ለሴቶች መብት ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት መሠጠቱንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት እየተደረገ ያለው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የጀርመን መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አምባሳደር ጌሳ ብራቲጋም በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል።

ሴቶችና ወጣቶችን ለማብቃትና የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለማጠናከር ሀገራቸው በትብብር እንደምትሰራና ድጋፍም እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.