ጠ/ሚ ዐቢይ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ዕለቱ ሃገራችን በታላቅ ጉጉት ለመስማት የምትጠብቀውን ብስራት የምትሰማበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያውያን የአመታት ልፋት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰበትና የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የተጠናቀቀበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በጋራ ጥረት ግድቡን እዚህ ደረጃ ስላደረስነው እንኳን ደስ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዕለት ኢትዮጵያውያን ዳግም ሃገር ተኮር ስራ ሰርቶ እንዴት ማሳካት እንደሚቻል አውቀናልም ብለዋል፡፡
የግድቡን ግንባታ ማንም ባላመነብን ወቅት በራሳችን አቅም ላይ እምነት ኖሮን ማሳካት መቻላችንም ይበልጥ አስደሳች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አንዳንዶች በህዳሴው ግድብ ላይ ሙጭጭ ማለታችን የታችኛውን የተፋሰሱን ሃገራት ለመጉዳት በማለም የተሰራ ስራ ይመስላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ የዚህ ትውልድ መለያ ማህተም፣ ሰርቶ የማሳካት ትዕምርትና የዘመናት ቁጭታችን መልስ ማግኘቱን የምናበስርበት ፋና መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አንገታችንን ሊያስደፉ ሲከጅሉን ለነበሩ ሁሉ የጫኑብን የድህነትና የኋላ ቀርነት ሸክም አሽቀንጥሮ ለመጣል መቁረጣችንን ጮክ ብለን የምንናገርበት ድምጻችን ነውም ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
ግድቡ ከእንግዲህ በሁለት እግራችን ለመቆም እንደማይሳነን ወደከፍታው ለማቅናት የመታጠፊያ ነጥባችን መሆኑን ዓለም በትክክል ይረዳል ብለው እንደሚገምቱም አውስተዋል፡፡
አሁን ላይም ማንንም ሳናስቸግርና ማንንም ሳንጎዳ የመጀመሪያውን ዙር ውሃ መሙላት መቻሉንም አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡ ለታችኛው የተፋሰሱ ሃገራት ከጉዳት ይልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ የተናገረችው አሁን እንደሚረጋገጥና ሲገነባም ሆነ ሲተዳደር ሱዳንንም ሆነ ግብጽን የመጉዳት አላማ እንደሌለም አስረድተዋል፡፡
ለዚህም የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ሁለቱ ሃገራት የሚያገኙት የውሃ መጠን ሳይቀንስ ማጠናቀቃችን ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ለህዳሴው ግድብ ስኬት ከመዋጮ ጀምሮ በሙያቸው፣ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው እንዲሁም በዓለም አቀፉ መድረክ በተደረገው ድርድር ለተሳተፉ አካላት እንዲሁም ለቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አሁን ላይም በተገኘው ድል ሳይኩራሩ የተሻለ ስራ መስራትና መሻገር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡