ዛሬ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን እጅግ ታሪካዊ ቀን ነው -ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የህዳሴ ግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት መጠናቀቅ በማስመልከት ለኢትዮጵያ ህዝብ የአንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ፕሬዚዳንቷ ባስተላለፏት መልዕክት ዛሬ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን እጅግ ታሪካዊ ቀን ነው ፤ ህልማችን እውን እየሆነ ነው ብለዋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን እና መሪዎች አባይን ለማልማት ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ዕቅዳቸው በተለያዩ መሰናክሎች ተስተጓጉሏል ያሉት ፐሬዚዳንት ሳህለወርቅ ነገር ግን «እኛ አሁን ባይሳካልንም መጪው ትውልድ ይገነባዋል» የሚል ታላቅ እምነት ነበራቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ትውልድ ያንን አደራ ጠብቋል ፤ ኃላፊነቱንም እየተወጣ ነው ፤ የሚጠራጠር ካለ ዛሬ ምላሹን አግኝቷል፡፡ ተፈጥሮም እንኳን ምስክርነቷን ሰጥታለች ብለዋል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፡፡
የሀገራችን ሀብት ከዜጎቿ አቅም፣ አንድነት እና ቁርጠኝነት ጋር እስከተቀናጀ ድረስ ምንም የማይቻለን ነገር የለም በማለት የገለፁት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከተባበርን፣ ለአንድ ዓላማ ከቆምን ምንም የሚያግደን ነገር የለም በማለት ገልፀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያ ለራሴ ብቻ ብላ አታውቅም ፤ ሁልጊዜም እንደምንለው የአባይን ውሃ መጠቀማችን በአካባቢው እህትማማች ሀገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮች እንዲጠናከሩ የተለየ ዕድል ይሰጣል እንጂ የመጠራጠርና የውድድር ምንጭ ጨርሶ ሊሆን አይገባምም ብለዋል።
አሁን ግድባችን ወደኋላ ሊመለስ እንደማይችል በተግባር መረጋገጡን ነው የተናገሩት።
ይህ እርምጃ አካባቢያችንን የሠላምና የመረጋጋት ምንጭ ለማድረግ ለሚተጉ ኃይሎች ሁሉ ታላቅ ድል መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳቷ ብስራቱም ለመላው የተፋሰሱ ሀገራት ህዝቦችም ጭምር መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሬዚዳንቷ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሥራች አባል እና ከ75 ዓመታት በፊት በቻርተሩ ላይ ፊርማዋን ያሳረፈች አገር መሆኗን በመግለፅ ድርጅቱ ከተቋቋመበት መርህ አፈንግጣ እንደማታውቅ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት፣ የጋራ ሠላምና ዕድገት ያላት ዘመናትን እንዲሁም መንግሥታትን የተሻገረ የማያወላውል አቋምና ተጨባጭ ተግባር ምስክር አያሻውም ብለዋል፡፡
የምናድገው አብረን ነው ፤ ቀጣዩ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነው የኃይል ማመንጨት ፍላጐታችን ያለጥርጥር እውን ሊሆን እንደሚችል ዛሬ አሳይቶናል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አይኖቻችን ከዚህ የመጨረሻ መዳረሻችን ሊነቀል አይገባም በማለት አሳስበዋል።
ግድባችንን ማጠናቀቅ ማለት ለዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ውል ማበጀት ማለት ነው ፤ ይህ ደግሞ ሁላችንንም ይመለከተናል ፤ በርካታ የቤት ስራዎች እንዳሉን አንዘንጋ ፤ ከፍታን እንመልከት ፤ከፍ ብለን እንመኝ ፤ ወደ ከፍታው የሚወስደን ላይ እናተኩር፤ አንድ ላይ በሆንንና በተባበርን ቁጥር ከአቅማችን በላይ የሚሆን የለም ሲሉ የአንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።