Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ በሰጡት መግለጫ፥  “ዓባይ ዛሬ እንደስሙ ሆነ፤ ዓባይ ትልቅ ማለት ነው። እስከ ዛሬ ግን አባይ አስቸጋሪ ነበር” ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የዓባይ ወንዝን የሺህ ዓመታት ታሪክ የቀየረ መሆኑን ያስታወቁት ርእሰ መሥተዳድሩ፥ “ከተሠራ የማይቀየር የለም፤ ዓባይን ከትሮ ለሀገር ጥቅም ማዋል ከተቻለ ሌሎችንም ሀብቶቻችንን ለሀገር ጥቅም ማዋል እንድንችል በር ይከፍታል”  ብለዋል።

የክልሉ ሕዝብና መንግሥት የዓባይ የማጠቃለያ ምዕራፍ የሆነውን ዘላቂ ተጠቃሚነትን በቀጣይነት ለማረጋገጥ ማንኛውንም የሚጠበቅባቸውን ተግባር ለማከናወን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው፥ የህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ የህዳሴ ግድብ ዛሬ ለተደረሰበት የስኬት ማማ መወጣጫ መሰላል ሆኗል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ አሻራ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌትን በማጠናቀቅ ደምቋል ያሉት አቶ ርስቱ፥ ተፈጥሯዊ መብትን ለመንጠቅ የተሯሯጡት ሀይሎች ህልም መንገድ ላይ ቀርቶ ትልቁ ድልም የኛ ሆኗል ብለዋል።

ይህ ደግሞ በአንድነት በቆምን ጊዜ የምንደርስበት ጫፍ ማሳያ እንደመሆኑ ሀይል አመንጭቶ ከድህነት ቅርቃሮች እስክንወጣ ጥረታችንም ይቀጥላል ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳደሩ ።

የሱማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድም፥ የህዝቦች የጋራ ጥረት ደማቅ አሻራን የታየበት የታሪክ ገድል ላይ ደርሰናል ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅም ከዚህ ቀደም በግድቡ ግንባታ ላይ ይነዛ የነበረውን አሉባልታ ያከሸፈ፤ ህዝብን ለማደናገር ይደረጉ የነበሩ ጥረቶችን ገመና ያሰጣ ስኬት ነው ብለውታል።

የመጀመሪያ የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅን የሰሙት የክልሉ ህዝቦች ሀሴት ላይ ናቸው ያሉት አቶ ሙስጠፌ ፥ በጋራ በመሆን እስከ ግድቡ መጠናቅቅ አስተዋጾቸውን ይቀጥላሉም ብለዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመጀመሪያ ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢንጅነር ታከለ ኡማ ባስተላለፉት የደስታ መግለጫ መልዕክት፥ “የዘመናችን የታሪክ ስኬት የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከወሳኝ ምእራፍ ላይ ደርሶ የመጀመሪያ ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል” ብለዋል።

“ሀገራችን ለዚህ ስኬት በመብቃቷ ለሁሉም ኢትየጵያውያን እንኳን ደስ ያለን ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፥  ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውኃ ሙሌት ላይ በመድረሱ መላው ኢትዮጵያዊያንን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

ግድቡ ባጋጠሙት ችግሮች ግንባታው መዘግየቱን ያስታወሱት አቶ አሻድሊ የውኃ ሙሌት እንዲጀመር የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያ ህዝብን በማስተባበር በአጭር ጊዜ ወስጥ የወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል ።

የግድቡ ውኃ ሙሌት መከናወኑ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ታላቅ መነቃቃትና ተስፋ መፍጠሩንም ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

በሀሰት ፕሮፖጋንዳው የተታለሉ ግለሰቦችን ግድቡ ተሽጧል የሚለውን ወሬ የከሸፈ መሆኑን በመረዳት ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ርእሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል ።

የጊዜ ጉዳይ እንጂ በለውጡ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ እየተጠናቀቁ የሀገራችን ብልፅግና የሚፋጠንበትና የለውጥ አደናቃፊዎች ደግሞ ወደ ኋላ የሚቀሩበት ጊዜ ቅርብ ነው ብለዋል ።

መላው ኢትዮጵያዊያን ግድቡን እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ርእሰ መስተዳድሩ  ጥሪ አቅርበዋል ።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.