Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ፥ “ለመላው ኢትዮጵያ ብሄሮች ፣ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች የህልውናችን መሰረት የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ውስብስብ ችግሮችን በማለፍ ገንብተን እነሆ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን” ብለዋል።

“ይህም እኛ ኢትዮጵያዊያን በብዝሃነታችን በአንድነት ስንቆም የማንመክተውና የማንሻገረው እንቅፋቶች እንደማይኖሩ ያሳየንበት የጽናታችንና የጥንካረችን መገለጫ ብቻ ሳይሆን፤ መንግስት በብሄሮች፣ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ብሄራዊ ክብርና ጥቅም ላይ የማይደራደር መሆኑን ምክር ቤታችን ይገነዘባል” ሲሉም ገልፀዋል።

ስለሆነም ግድቡ እስኪጠናቀቅና የመጨረሽ ሪቨን እስኪቆረጥ በተጀመረው ሀገራዊ መነቃቃት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በራሳቸው ስም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር አብረሀም በላይ በበኩላቸው፥ “የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ስላጠናቀቅን እንኳን ደስ አለን” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዶክተር ኢንጂነር አብረሀም፥ “የህዳሴው ግድብ ከጥንስሱ ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ድረስ ብሎም እስኪጠናቅቅ ድረስ የተግባር ተመሳሌትነቱ በታሪክ ምሁራን በተደጋጋሚ ግዜ የሚነሳውንና የናይል ውሀ ከአመታት በኋላ የአገራት ግጭት መንስኤ ይሆናል የሚለውን የስጋት ትንተና የሚገዳደር፤ በተቃራኒውም በሀገራት መካከል መተማመንና መተባበር እድል ከተሰጠው ተአምራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚያስረዳ አዲስ በታሪክ ከዚህ በፊት ያልነበረ የውይይት አድማስ የሚያስተዋውቅ ሲሆን፤ ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ሙሌትም ጠንካራ የጉዳዩ ፀሐፊዎችን ወደ መስኩ በትብብር መነፅር ፍተሻ እንዲያማትሩ ከኢትዮጵያውያንና ከመንግስታቶቻቸቸው በተለየ ለሱዳን እና ግብፅ ሕዝብ የተበረከተ የወንድማማችነት የመተማመን እና የመተባበር ተነሳሽነት ገፀ በረከት በተግባር ሆኖ ጉባ ላይ መቆሙን አፍ አውጥቶ ይናገራል” ብለዋል።

“በእስከአሁኑ ሒደት ፕሮጀክቱን ከመጠንሰስ ማለትም ከንጉሱ ግዜ ጀምሮ በኋላም ደፍረው የጀመሩትን በሒደት ቅብብሎሹም ፕሮጀክቱን የመሩትን መሪዎቻችንን እና አሁንም ብዙ ጫና እየሰሩ ያሉ ከፍተኛ የፖለቲካዊ አመራሮቻችን ዲፕሎማቶቻችንና የፊት መስመርና የደጀን የድርድር ሰዎቻችንን ሚዲያዎቻችንን ያለመታከት በመስዋእትነትም ጭምር ለፕሮጀክቱ የደከሙና በመስራት ላይ ያሉ የፕሮጀክት አመራሮቻችን እና በልዮ ልዮ የሙያ ዘርፍና በጉልበትም እያገለገሉ ያሉትን ነገን በፅኑ ተስፋ አድርገው ከመቀነት እስከ ካዝና ሀብትና ጉልበታቸውን ያለ ስስት በቦንድ ግዢና በልገሳ የሰጡና እየሰጡ ያሉትን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሐይማኖት መሪዎቻችንና የሐገር ሽማግሌዎች ወጣቶቻችንና ሴቶቻችን ምሁራኖቻችን የከበረ ምስጋና ይድረሳችሁም” ብለዋል።

እንዲሁም ግድቡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊደርስ የሚችለውን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ቀንና ሌሊት ያለእረፍት እየሰሩ ላሉ የደህንነትና የፀጥታ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የዉሃ ሙሌት መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰማውን ደስታ የገለፀ ሲሆን፥ ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ ሲል መልእክቱን አስተላልፏል።

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ለመላ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት ደስታ በታላቅ ገልጿል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ባስተላለፉት መልእክት፥ “በታሪክ ፊት እንደ አደዋ ድል ገኖ ለተከታይ ትውልድ የሚደርሰው ይህ አንፀባራቂ የዘመኑ ትውልድ አሻራ ለመላ ኢትዮጵውያን ወደር የለሽ ደስታን ያጎናጸፈ” መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ታሪካዊ ክስተት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላ አፍሪካውያንና በገዛ ሃብታቸው እንዳይጠቀሙ ለተገፉ የዓለም ህዝቦች የይቻላልን መንፈስ የሚያጎናጽፍ በመሆኑ የአገራችንን ገፅታ በዓለም መድረክ ከፍ አድርጎ ከማሳየቱ ባሻገር በቀጣይ ጊዜያት የዓለም ህዝቦች ይህንን ተሪካዊ ግድብ ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ እንዲጎርፉ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.