በደረስንበት የስኬት ምዕራፍ ሳንታጠር፤ ድላችንን እያጣጣምን ለላቀ ድል መነሳት ይኖርብናል- ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደረስንበት የስኬት ምዕራፍ ሳንታጠር፤ ድላችንን እያጣጣምን ለላቀ ድል መነሳት ይኖርብናል አሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም፥ “እነሆ! የሃገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ዓመታት ለፕሮጀክቱ ስኬት ተሳትፏቸውን በተለያየ መልክ የገለፁበት እና ግንባታው ለአፍታ እንዳይገታ የባለቤትነት ስሜታቸውን በቁጭት ያንፀባረቁበት ታሪካዊ የውሃ ሙሌት ምዕራፍ በስኬት በመጠናቀቁ – እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን” ብለዋል።
በቀጣይም በተቀናጀ የተፋሰስ ስራ የግድቡን ጤንነት የመጠበቅ፤ የግንባታ ስራዎችን የማከናወን፤ የዕውነትን መንገድ በማጥበቅ የተፈጥሮ ፀጋችንን ፍትሃዊ በሆነ አግባብ የመጠቀም እና የታችኛው ተፋሰስ ሃገራትን ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።
“በደረስንበት የስኬት ምዕራፍ ሳንታጠር፤ ድላችንን እያጣጣምን ለላቀ ድል መነሳት ይኖርብናል” ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።