ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን እንዳትጠቀም ይደርስባት የነበረውን የፍትህ ማጣት የግድቡን የውሃ ሙሌት በማከናወን ታላቅ ገድል ተፈጽሟል- አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን እንዳትጠቀም ይደርስባት የነበረው የፍትህ ማጣት፤ የግድቡ የውሃ ሙሌትን በማከናወን በጋራ ጥረት ታላቅ ገድል ተፈጽሟል አሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥበብ በተሞላበት የዲፕሎማሲ ጥረት በጋራ በመቆም የውሃ ሙሌቱ መከናወኑ ድል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከቀኝ ግዛት መገፋት እስከ ካይሮ ሰዎች ተፈጥሯዊ መብቷን እስከመቀማት የደረሰ በደል እንደነበረም አስታውቀዋል።
አቶ ኃይለማርያም ከዚህ ጋር በተያያዘም፥ “የህዳሴው ግድብ ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ ሳስብ ስለ ሶስት ጉዳዮች የሚሰማኝ ስሜት አለ” ብለውናል።
አሁን በህይወት ከሌሉት የቀድሞ የግብፅ ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ ጋር ለብቻቸው ተገናኝተው ያሏቸው ነገርን እና ሙርሲ ዛሬ በህይወት ኖረው የግድቡን ሁኔታ ቢያዩትም ይመኙ እንደነበር አንስተዋል።
ሙርሲ ሲታወሱ ኢትዮጵያ ላይ ጦር ስለማወጅ እየተወራ የተለቀቀው ቪድዮ የሚታወስ ነው፤ አቶ ኃይለማርያም ግን ያ የግብፅ ዛቻ የተሰማው መሀመድ ሙርሲ ከኔ ጋር ካወሩ በሁኋላ ነው ሲሉም ይናገራሉ።
የአሁኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲ ሲ ጋር በተያያዘም አቶ ኃይለማርያም፥ አጀማመራቸው ላይ ቅን ቢመስሉም የተለደመው የግብጽ አቋም ላይ ቀጥለዋል ብለዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ነገሩን በቅንነትና በጋራ ተጠቃሚነት ስለያዘችው አሸናፊ መሆኗንም ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ የፍትህ በርም ተከፍቷል ያሉት አቶ ኃይለማርያም፥ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝን እንዳትጠቀም ይደርስባት የነበረውን የፍትህ ማጣት፤ የግድቡ የውሃ ሙሌትን በማከናወን በጋራ ጥረት ታላቅ ገደል ተፈጽሟል ሲሉም ተናግረዋል።
በህዝቦች የጋራ ጥረት እና አቋም ህዳሴዋ እውን መሆን ጀምሯል ሲሉም ገልፀዋል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፥ በትውልድ ቅብብሎሽ ብሄራዊ ፕሮጀክቱ እዚህ ያደረሱትን መሪዎችንም ያመሰግናሉ።
ለህዳሴው ግድብ ግንባታ መጀመር ትልቅ ሚና ላላቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም አድናቆታቸውንም ገልጸዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙርያ በቅርቡ ያጋጠሙ የዲፕሎማሲ ውጥረቶችን አስመልክቶ አቶ ሀይለማርያም ሲናገሩም፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጉዳዩን በጥበብ ይዘውታል ብለዋል።
የህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ ፕሮጀክቱ በውጣውረዶች ውስጥም ቢሆን ለተደረሰበት ውጤት ጉልበት ሆኖታልም ብለዋል ።
ሆኖም አሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም፥ የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት አይን መግለጥ ያህል የሚገለጽ እንደመሆኑ፤ በቀጣይ በድርድሩም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ከህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በሀይለየሱስ መኮንን
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።