Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ28 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተወረሰ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 28 ሺህ 608 ሊትር ቤንዚንና ናፍጣ መወረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሀላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፤ ለከተማዋ እየቀረበ ባለው ነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭት እና ቁጥጥር ሂደትን በሚመለከት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው አንስቶ የክትትልና ድጋፍ ስርዓት ተዘርግቶ እየተመራ መሆኑን አንስተዋል፡

በዚህም በከተማዋ 125 ማደያዎች ናፍጣ በአማካኝ በቀን 2 ሚሊየን፣ ቤንዚን በአማካኝ በቀን 1 ነጥብ 45 ሚሊየን ሊትር በድምሩ ባለፉት ስድስት ወራት በቀን በአማካኝ 3 ነጥብ 45 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡

በቁጥጥር ሂደት ህገ-ወጥ ተግባር ውስጥ የገቡ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው፤ በዚህም በህገ-ወጥ ሲዘዋወር የተወረሰ የነዳጅ መጠን ቤንዚን 18 ሺህ 985 ሊትር፣ ናፍጣ 9 ሺህ 434 ነጥብ 5 እና ነጭ ጋዝ 189 በድምሩ 28 ሺህ 608 ነጥብ 5 ሊትር ነዳጅ መወረሱን ተናግረዋል፡፡

የዋጋ ጭማሪ በመጠባበቅ ሳይሰራጭ የቆየ አንድ ቦቲ ቤንዚን የዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ በመደበኛው ገበያ 19 ሺህ ሊትር እንዲሸጥ በማድረግ ጭማሪው ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡

በጥቅሉም 47 ሺህ 608 ነጥብ 5 ሊትር ነዳጅ ምርቱ ተሽጦ 2 ሚሊየን 600 ሺህ 649 ብር ከ94 ለመንግስት ገቢ መደረጉም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ቢሮው የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭቱን ጤናማ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አበክሮ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ነዳጅን በኮንትሮባንድ በመሸጥ ከከተማ እንዲወጣ የሚያደርጉ ማደያዎች ላይና ከኤሌክትሮኒክስ የመገበያያ አማራጮች ውጪ ነዳጅን በጥሬ ገንዘብ ሽያጭ የሚፈጽሙት ላይ ቢሮው ጠበቅ ያለ ርምጃ ይስዳል ተብሏል፡፡

በማደያቸው የሚገኙ ማሽኖችን ሁሉንም አገልግሎት ላይ ባለማዋል ተገቢ ያልሆነ ሰልፎችን የሚፈጥት ላይና በንግድ ፍቃድ አሰጣጥ መስፈርቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የ24 ሰዓት አገልግሎት በማይሰጡ ማደያዎች ላይ በህጉ በተቀመጠው አግባብ ርምጃ እንደሚወሰድ ቢሮው አሳስቧል፡፡

ማደያዎች በመንግስት የሚቀርበውን ነዳጅ ስርዓቱን በጠበቀና በህጋዊ አግባብ ማሰራጨት እንደሚገባቸውና ማህበረሰቡም ይህን አውቆ አገልግሎቱን በፍትሀዊነት ማግኘት እንዲችል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ መልዕክት ተላልፏል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.