የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስማርት ኮርት ሲስተምን ለመተግበር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት ፈረመ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስማርት ኮርት ሲስተምን ተግባራዊ ለማድረግ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው፣ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አቶ ዓለምአንተ አግደው በወቅቱ÷ ስማርት ኮርት ሲስተሙ የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ፈላጊዎች እርካታ በማሳደግ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ግልጽ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ያግዛል ብለዋል።
ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው÷ ኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ፈላጊ ዜጎችን ሕይወት ቀላል ለማድረግ ለዲጂታላይዜሽን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመደበኛ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር ተቋማቸው ዲጂታል ኢትዮጵያን ዓልሞ እየሰራ መሆኖን ጠቅሰው÷ በእያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የፍትህ ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ማድረግ የዜጎችን የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበት ብክነት በመቀነስ ምቹና ግልጽ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላልም ነው ያሉት።
በደሳለኝ ቢራራ