Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ የሀገር ሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ የሀገር ሉዓላዊነት ማረጋገጫ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢዜማ፣ ኢሀፓ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲዎች ግድቡ ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስጠብቅ፣ የሀገርን ጥቅም ለሌላ አሳልፎ ያለመስጠት ምሳሌ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢሀፓ ፓርቲ ዋና ፀሀፊ አቶ ቴዎድሮስ ደግሞ ስኬቱ ሌሎች ሀገራትን ከድህነት ሊያላቅቁ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

የህዳሴው ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ እና በራስ አቅም እየተገነባ መሆኑም ቀጠናዊ ተሰሚነትን እንደሚያጠናከር የተናገሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ይህን ከጫፍ ለማድረስ ደግሞ ልዩነቶችን ወደ ኋላ ማለት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

አሁን ያለበት ደረጃ እና በራስ አቅም መገንባት መቻልም ቀጣይ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ማሳያዎች መሆናቸውንም አውስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ እንደ ከዚህ በፊቱ ግንባታውን ከጫፍ ለማድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

ግድቡ ሲጀመር በአንድነት የተነሳው የኢትዮጵያ ህዝብም አሁን ላይ ለመድረሱ አንድ በመሆን እና ለሀገሩ ቅድሚያ በመስጠቱ መሆኑን ያነሱት አመራሮቹ በቀጠናው ያለንን ተሰሚነት ከዚህ በላይ ከፍ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ሁሉም የበኩሉን መወጣት እና የግዱቡን ግንባታ ከጫፍ ለማድረስ በጋራ ከመንግስት ጎን መቆም እና ድጋፉን ማጠናከር እንደሚገባውም አሳስበዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.