Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ማጥበብንና እርቅ ማስፈንን ቁልፍ የሰላም አማራጭ አድርጎ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ማጥበብንና እርቅ ማስፈንን ቁልፍ የሰላም አማራጭ አድርጎ እየሰራ ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፤ መንግስት ሰላምን ለማረጋገገጥ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፤ በተለይም በተለያየ ምክንያት ነፍጥ ያነሱ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ እንዲያቀርቡ ሁሉም የሰላም በሮች ለሁሉም ሃይሎች እኩል ከፍቷል ብለዋል፡፡

በዚህም በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት በመፈጸም ወደ ሰላማዊ ህወታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

በቅርቡም በተደረገ የማሟያ ምርጫ በቤንሻንጉልል ጉሙዝ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የተወሰኑ ሃይሎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘት መቻላቸውን አስታውሰዋል።

ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር የነበረውን ግጭት በፕሪቶሪያው ስምምነት በመደምደም ስምምነቱን በተሟላ መንገድ ለመተግበር መንግስት ያላሳለሰ ጥረት እያደረገ ነው አጠናክሮም ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

መንግስት የተለያየ ፍላጎትና የፖለቲካ ሃሳብ ካላቸው አካላት ጋር ገንቢ ውይይቶችን በማድረግ መግባባት ላይ የደረሰባቸውን ጉዳዮች ለማጎልበት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

መንግስት ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለማጥበብና እርቅ ለማስፈን እንዲሁም የቀድሞ ታጣቂዎች በተሃድሶ ስልጠናዎች አልፈው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግን ቁልፍ የሰላም አማራጭ አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

በቅርቡም በኦሮሚያ እና በአማራ  ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በብዙ ሺህ  የሚቆጠሩ ታጣቃዊዎችና አመራሮቻቸው  የሰላም ጥሪን ተቀብለው በመግባት የተሃድሶ ስልጠናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

 

በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሰላም ወዳዶች ስልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፤ ስልጠናውን በውጤታማነት እንዳጠናቀቁም ወደ ህብረተሰቡ እንደሚቀላቀሉ አስገንዝበዋል፡፡

 

እንዲሁም  መንግስት በሶማሌና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች በሰላማዊ ንግግር እንዲፈቱ  ጥረት ማድረጉን ገልፀው ፤በዚህም በአካባቢዎቹ ሰላም እና መረጋጋት መስፈኑን ተናግረዋል፡፡

 

ሰላምን የማስፈን ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉም ነው ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) የተናገሩት፡፡

 

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.