ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ ከ15 ነጥብ 9 ሚሊየን ዩሮ በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) ኢትዮጵያና ኔዘርላንድስ ከ15 ነጥብ 9 ሚሊየን ዩሮ በላይ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን ለቁንዝላ የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር እና የዋሽ ፕሮግራምን ለመደገፍ የሚውል ነው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ በዋናነት በአካባቢው ያለውን ማህበረሰብ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል ነው የተባለው፡፡
በአካባቢው የግብርና ምርታማነትን ማሳደግና ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ማህበረሰብ አቀፍ የሆኑ ተቋማትና ድርጅቶችን አቅም ማጠናከር፣ ዘላቂ በሆነ መልኩ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት መጠበቅና ማስተዳደር የድጋፉ አካል ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ማህበረሰብ አቀፍ የሆኑ የውሃ አካላትን መንከባከብ እንዲሁም በከተማና በገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማዳረስና የፍሳሽና ንጽህና አጠባበቅን ማዘመን የድጋፉ አካል መሆኑም ተገልጿል፡፡
በፕሮጀክቱ በተለይም በአካባቢው የሚኖሩ 22 ሺህ አርሶ አደሮችን ምርታማነት በማሳደግ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በአካባቢው የሚኖሩ 750 ወጣቶች በዚህ ፕሮጀክት በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት አማካኝነት እንደሚተገበር ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡