አቶ አሕመድ ሺዴ ከእስያ መሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከቻይና ጉብኝታቸው ጎን ለጎን ከእስያ መሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያዩ፡፡
በዚሁ ወቅትም በኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ መኖሩን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በመንግሥት በኩል እየተሰሩ ያሉ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በኢኮኖሚው ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እየተከናወነ ያለውን ሥራ ገልጸዋል፡፡
የእስያ መሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ራጃት ሚስራ በበኩላቸው÷ በቅርቡ በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት እየተሰሩ ባሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መደነቃቸውን አንስተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማየት እንደሚመጡ እና ትብብራቸውን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡
በአቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በቻይና የሥራ ጉብኝት ማድረጉን እንደቀጠለ መሆኑን በሀገሪቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
ልዑኩ እያደረገ ባለው ቆይታ እስከ አሁን ከቻይና ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ፣ ከቻይና ልማት ባንክ፣ ከቻይና ኮሙኒኬሽንና ኮንስትራክሽን ኩባንያ እንዲሁም ኤግዚም ባንክ ኃላፊዎች ጋር ውይይ አድርጓል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያና ቻይናን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በአቤል ንዋይ