Fana: At a Speed of Life!

መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማኅበር የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲጠናከር ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መቄዶኒያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማኅበር ጤና ሚኒስቴር የተለያዩ አካላትን በማስተባበር እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቀ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከመቄዶኒያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማኅበር መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ማኅበሩ ለአረጋውያን እያደረገ የሚገኘው ክብካቤ እንደሀገር በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት አሳድጓል ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የጤና ፖሊሲ የአረጋውያን እና አእምሮ ህሙማን ሕክምና ከመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና መስጫ ተቋማት ጀምሮ እንዲሰጥ ለማድረግ ማስቻሉ ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል፡፡

ተቋማቸው ለማኅበሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

የማኅበሩ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው÷ ማኅበሩ እራሳቸውን ችለው መታከም የማይችሉ እና የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ህሙማንን በማንሳት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመሥግነው በቀጣይም ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ማኅበሩ እያስገነባው የሚገኘው 1 ሺህ 200 አልጋዎች የሚኖሩት ሆስፒታል ግንባታን ለማጠናቀቅ እና የሕክምና መሳሪያዎችን ለሟሟላትም ከሚኒስቴሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ በውይይቱ ወቅት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በቀጣይ የማኅበሩን ስራ በዘላቂነት ማስቀጠል በሚቻልበት መንገድ ዙሪያም ምክክር አድርገዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.