በአገልግሎትና አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችን በመሰረታዊነት ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ትግበራና የዝግጅት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አመራር ዐቢይ ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ መካሄዱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በውይይታቸውም ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና በመጀመሪያ ዙር የተመረጡ ተቋማት ያከናወኗቸውን የሪፎርም ሥራዎች መገምገማቸውን አንስተዋል፡፡
የሪፎርም አስተዳደራዊ ሥራዎች፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሥርዓትን መዘርጋት፣ የዲጂታል ሲቪል በመገንባት አገልግሎቶችንና ውሳኔዎችን ማቀላጠፍ ላይ ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውንም ተመልክተናል ብለዋል።
በሪፎርሙ የታቀፉ ተቋማትም ያላቸውን ልምዶች የሚቀያየሩበት እና ተቀራርበው የሚሰሩበትን አውድ መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ተቋማት ያከናወኗቸውን ተግባራት በዝርዝር በመቃኘት ጥንካሬዎችንና ውስንነቶችን ለይተናል ያሉት አቶ ተመስገን÷ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ አስቀምጠናል ሲሉ አመላክተዋል፡፡