Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተፋሰስ ልማት ስራ ንቅናቄ ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ “የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን!” በሚል መሪ ሀሳብ ለ30 ቀናት የሚከናወነውን የዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ቀበሌ አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በጎፋ ዞን የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ልብ ሰባሪ መሆኑን አስታውሰው ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት ዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር)÷ በዞኑ 183 ንዑስ ተፋሰስ ውስጥ ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍንና የአካባቢውን ሁኔታ ያገናዘበ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ፥ ባለፉት አምስት አመታት በማሕበረሰብ ተፋሰስ ከ711 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ገልፀዋል።

በዚህ የተፋሰስ ልማት ስራም በ421 ሺህ 378 ሄክታር በላይ መሬት ለሚቀጥሉት 30 ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድና ከ2 ነጥብ 39 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል፡፡

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.