በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአፈር እና ውሃ ጥበቃ አካል የሆነው የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡
የማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር እንዲመለስ በማገዝ የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነት እንደሚያሳድግ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ በንቃት ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በመርሐ ግብሩ በ53 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራውን በስኬት ለማከናወን ለግብርና ባለሙያዎች እና ቀያሽ አርሶ አደሮች ሥልጠና መስጠትን ጨምሮ አስፈላጊቅ ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ መገለጹ ይታወሳል።
በመርሐ ግብሩ 247 ሺህ ዜጎች የሚሳተፉ ሲሆን÷ ለሥራው የሚውሉ የቁፋሮና ሌሎች መሳሪያዎች ዝግጁ ተደርገዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሚከናወንባቸው 429 በላይ ተፋሰሶች ተለይተዋል።