የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ሲያካሂዱት የነበረውን ውይይት ማብቂያ አስመልክቶ ችግኝ ተከሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት ማብቂያ አስመልክቶ ችግኝ ተከሉ፡፡
ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ናቸው ዛሬ ከወረዳ እስከ ማእከል ድረስ ሲያካሂዱ የነበረውን ውይይት ማጠቃላያ አስመልክቶ እንጦጦ አካባቢ የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት ያካሄዱት፡፡
ስነ ስርዓቱም መታሰቢያነቱ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለህዝቦች አኩልነት በፅናት ለታገለውና ሰኔ 22 ቀን 2012 ሕይወቱ ላለፈው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መሆኑ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በውይይቱ ላይ የጉለሌ ክፍለ ከተማ አመራሮች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ200ሺህ በላይ ብር ስጦታ ማበርከታቸውን ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በስነስርዓቱ ላይ ÷ ይህ ወቅት አባይ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት ለሆኑት ኢትዮጵያውያን እጅ የሰጠበትና ትውልዱ ታሪክ የሰራበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡
ይህ አመራርም በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ ባካሄደው ውይይት ህብረተሰቡን ይበልጥ ለማገልገልና ችግሮችን በከፍተኛ ተነሳሽነት ለመሻገር ለራሱ ቃል የገባበት ወቅት መሆኑን መናገራቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አመራሮቹ በወቅታዊ ጉዳዮች ፤ባለፈው አንድ አመት የነበረ አፈፃፀምና በሀገራዊና ከተማዊ የፖለቲካ አጀንዳዎች ዙርያ ውይይት አካሂደዋል፡፡