ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የህዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕምባ ጠባቂ ሆነው ተመረጡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕምባ ጠባቂ ሆነው ተመረጡ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባው ምርጫውን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ ምክትል ዕምባ ጠባቂ እና የዘርፍ ዕምባ ጠባቂ ምርጫንም በተመሳሳይ መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን የኔነህ ስመኝ (ዶ/ር) ምክትል ዕምባ ጠባቂ ሆነው ተመርጠዋል።
አቶ አባይነህ አዴቶ ደግሞ የዘርፍ ዕምባ ጠባቂ ሆነው በምክር ቤቱ ተመርጠዋል።
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ምርጫውን አስመልክቶ እንደገለጹት÷ ምክር ቤቱ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 13/2016 አንቀጽ 11 መሰረት እጩ አቅራቢ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡
እጩ አቅራቢ ኮሚቴው ግልጽነት በተሞላበት መንገድ በሚቀርብ ይፋዊ የህዝብ ጥቆማ መሰረት እጩዎች ተወዳድረው ለምክር ቤቱ እንደሚቀርቡ ምክር ቤቱ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት ዋና ዕምባ ጠባቂ የነበሩትንና የሥልጣን ጊዜያቸው የተጠናቀቀውን እንዳለ ኃይሌን (ዶ/ር) የሚተኩት ወ/ሮ ስመኝ በስርዓተ ጾታ የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን÷ የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው እንዳገለገሉ ተገልጿል፡፡
ምክትል ዕምባ ጠባቂ ሆነው የተመረጡት የኔነህ ስመኝ (ዶ/ር) ደግሞ በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድር ዋና የህግ አማካሪና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ዳኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡
እንዲሁም የዘርፍ ዕምባ ጠባቂ ሆነው የተመረጡት አቶ አባይነህ አዴቶ÷ በደቡብ ኢትዮጵያ የፍትህና ህግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል ተብሏል፡፡
በአሸናፊ ሽብሩ እና የሻምበል ምህረት