የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እድሎች ለጃፓን ባለሃብቶች የማስተዋወቅ ስራ ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፀጋዎችና የኢንቨስትመንት እድሎችን ለጃፓን ባለሃብቶች የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት የንግድና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ተዘጋጅቷል፡፡
ከጃፓን የመጡ 50 ባለሃብቶችና ከኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ አባላት በመድረኩ ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ የቱሪዝም ፀጋዎችና የኢንቨስትመንት እድሎችን በተመለከተ ገለፃ ተደርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም ሃብት፣ ሰፊ የመልማት እድልና መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት መነሻ በማድረግ በቱሪዝም ዘርፍ ፈርጀ-ብዙ የኢንቨስትመንት እድሎችና አማራጮች መኖራቸውም ተገልጿል፡፡
የጃፓን ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩና የቱሪዝም መስህቦችን እንዲጎበኙም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ እንደገና አበበ (ዶ/ር)÷ ባለሃብቶች በቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት የሚችሉባቸው ሰፊ እድሎች መኖራውንና ለዚህም ተቋማቸው ጋር በትብብር አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም ልዑካን ቡድኑ የብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ሙዚየምን እንደጎበኘም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡