ለውጡን ተክትሎ በፍትህ ዘርፉ ላይ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች ተከናውነዋል-ወ/ሮ ሃና አርዓያ ስላሴ
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለውጡን ተክትሎ በፍትህ ዘርፉ ላይ መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች ተከናውነው በርካታ ስኬቶችም መመዝገባቸውን የፍትህ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያ ስላሴ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ በለውጡ ዓመታት በፍትህ ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትንና የተገኙ ስኬቶችን በማስመልክት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎች በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ መጠናከር ትልቅ መሠረት ያኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ሚኒስቴሩ ሕገ-መንግስቱን እና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማክብርና ማስከበር፣ የህግ-የበላይነት ማስፈን፣ የወንጀል ሕግን ማስከበርና ማስፈጸም እንዲሁም የመንግስትንና የህዝብን ፍትሐ ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር በሚል የተሰጡትን ዋና ዋና ኃላፊነቶች እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም የሕግ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቁመው ለህዝብ የቅሬታ ምንጭ የሆኑና መብቶችን የሚገድቡ ህጎችን በመለየት የማሻሻል ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አፋኝ የነበሩና የግለሰብ መብቶችን የሚገድቡ መብቶችን የማሻሻልና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት አስፈላጊ የሆኑ ህጎችን በመለየት ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም የጸረ-ሽብር ሕግ ላይ መሰረታዊ ማሻሻያ መደረጉን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው ሕግ፣ የመገናኛ ብዙሃን ሕግን በማሻሻል ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የወንጀል ስነ-ስርዓትና ማስረጃ ሕግ መድብልም አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባና አሁን ላለው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር አመቺ የሆነ አስተዳደራዊ ህግ ተረቅቆ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመጽደቅ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በሌላ መልኩ የግልግል ዳኝነትን የሚመራ ህግ በአዲስ መልክ መውጣቱን ጠቁመው ክርክሮችን በግልግል እና በሌሎች አማራጮች በመፍታት ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና የሚያስቀር መሆኑን አክለዋል።
የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነትን የሚያረጋግጡ ህጎች መውጣታቸውንና በዚህም ለኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት እውቅና የሰጠ አዋጅ እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አማኞች ካውንስልን ያቋቋመ አዋጅ ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር የወጡ ህጎችም በህግ ማሻሻያ ላይ ከተሰሩ ስራዎች ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከል በተሰራው ስራ ከፖሊስ ጋር በመተባበር የማጣራት ስራዎችን በመስራት የወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተጠያቂነትን ማስፈን መቻሉን እንዲሁም የኢኮኖሚ ወንጀሎችን የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች እንደተሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡