Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል – ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሯ ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና የጸጥታ ችግሮችን በመቋቋም ኢኮኖሚው ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

የተመዘገበው ዕድገት ኢትዮጵያን በዓለም በተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ እንዳሰለፋት ገልጸው፤ ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ፣ ከሰሃራ በታች ሶስተኛ እንዲሁም ከአፍሪካ አምስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ተችሏል ብለዋል።

መንግሥት የገቢ አሰባሰቡን ከማጎልበት ባሻገር የተከማቸውን ዕዳ ለመቀነስ ባለፉት አምስት ዓመታት 10 ቢሊየን ዶላር ብድር ተመላሽ ማድረጉን አንስተዋል።

በዚህም የውጭ የዕዳ ጫና ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ከለውጡ በፊት የነበረው የ30 በመቶ ምጣኔ አሁን ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ መውረዱን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በየዓመቱ በአማካይ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ መሳብ መቻሉን እንዲሁም በግብርና የማዕድን፣ የቱሪዝም፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት መጨመሩንና የቱሪዝም መሰረተ ልማት መስፋፋቱን አብራርተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲኖር ማስቻሉንና ባለፉት ስድስት ወራት ባንኮች ከሸጡት የውጭ ምንዛሬ የገዙት እንደሚበልጥ ተናግረዋል።

በዚህም ተለዋዋጭ የዋጋ ሁኔታዎች በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥሩ ለደመወዝ፣ ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያና ሌሎች መሰረታዊ ድጎማዎች ከ400 ቢሊየን ብር በላይ መመደቡን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.