ኢትዮጵያ ለህብረቱ አጀንዳ 2063 መሳካት ሁለንተናዊ ድጋፍ ታደርጋለች- ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እንደ አንድ አባል ሀገር እንዲሁም የህብረቱ መቀመጫ እንደመሆኗ ለአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 መሳካት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ የሚገኘውን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) በጎበኙበት ወቅት ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ከዶ/ር ጃን ካሴያ ጋር ተወያይተዋል።
ጌዲዮን(ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር እየተሠሩ ላሉ ሥራዎች የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አስተናጋጅ ሀገር ለአፍሪካ ህብረት ተቋማት ትልሞች መሳካት የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ጨምሮ ከዚህ በፊት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ጃን ካሴያ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) የደረሰበትን ተቋማዊ ዕድገት ያስጎበኙ ሲሆን የህብረተሰብ ጤና አገልግሎት ለማሳደግ እና ደረጃውን የጠበቀ የጤና ምርምር እና ጥናት ለማከናወን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለማዕከሉ መጠናከር የምታደርገውን ድጋፍ እንድትቀጥልም መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡