ሀገራዊ ወጪን በራስ የገቢ አቅም መሸፈን የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ ነው – ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሀገርን ወጪ በራስ የገቢ አቅም መሸፈን የሚችል ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ለውጡን ተከትሎ የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች በገቢ አሰባሰብና አስተዳደር ሥርዓቱ ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ብልፅግና ፓርቲ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሰጠው ትኩረት በገቢ ዘርፍ በ2022 የሀገርን ወጪ በራስ አቅም የመሸፈን ርዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው ብለዋል።
በፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ ጠንካራና ጫናን የሚቋቋም ኢኮኖሚ ለመገንባት የሀገር ውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በነበረው ዝቅተኛ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት በተወሰደ ማሻሻያ እርምጃ እመርታዊ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል።
በ2014 ዓ.ም 336፣ በ2015 ዓ.ም 442 እና በ2016 ዓ.ም 512 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተዋናዮች የሚከፍሉት የገቢ ግብርም የጋራ መሰረተ ልማቶችን በፍትሕዊነት ለመገንባት አዎንታዊ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የተሟላ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት ሥርዓትን በመፍጠር የገቢ አቅምን ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ወጪ በራሷ ገቢ መሸፈን የሚችል ጠንካራ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 900 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት ስድስት ወራት 451 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብስብ መቻሉን ተናግረዋል።
በገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት የተቀመጠውን ርዕይ ማሳካት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በታክስና ጉምሩክ አስተዳደር ሕግጋት መነሻነት ዜጎች በሚያመነጩት ገቢ ልክ ግብርን በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት የሚያስችሉ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።
የግብር ከፋዮች ታክስን የማሳወቅ ልምምድ እያደገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በግብር ከፋዩና ተቋሙ መካከል የሚስተዋልን የሒሳብ ልዩነት ለማጥበብ የሚሰጠው ትምህርትና ስልጠና ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን የሚገነዘብ የሰው ሃይል በመገንባት በዲጂታል ኢትዮጵያ ርዕይ ስር ግብር ከፋዮች በዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ያለእንግልት በኦላይን የሚከፍሉበት ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም በ2013 ዓ.ም 5 ሺህ 901 የኦላይን ግብር ከፋይ ከነበረበት በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት 48 ሺህ 349 ግብር ከፋዮች በኦላይን ማሳወቅ የቻሉበት አቅም እንደተፈጠረ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።