መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠቀማቸው ከፍተኛ ወጪ ማስቀረቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ በአግባቡ መጠቀማቸው ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት መቻሉን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ተቋሙ ከእቅድ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተገልጿል።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ የድርጅቱን እና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም ከሁለት ሚሊየን ቶን በላይ ጭነት በባህር ተጓጉዟል።
በዩኒሞዳል የትራንስፖርት ስርአት ከ654 ሺህ ቶን በላይ ገቢ እቃ እና ከ174 ሺህ ቶን በላይ ወጪ እቃ ማስተናገድ መቻሉን ጠቁመው፤ በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከተሰጡ አገልግሎቶች እና ከሌሎች የገቢ ምንጮች ከ46 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
በወጪ ንግድ ላይ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን እና ለረጅም ጊዜ ሳይዘጉ የቆዩ ሂሳቦችን መዝጋት ተችሏል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ያልተሰበሰቡ ሂሳቦችን በመሰብሰብ ረገድ ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠሩ የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ በአግባቡ በመጠቀማቸው ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት መቻሉን ጠቁመዋል።
የኮንቴነሮችን የወደብ ቆይታ ለመቀነስ የተከናወነው ስራ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ማስረዳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።