የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ለብልጽግና ፓርቲ 2ኛ ጉባዔ የድጋፍና የመልካም ምኞት መልዕክት ላከ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የድጋፍና የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ (ሲፒሲ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በመልዕክቱ÷በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ላለው ሁለንተናዊ እድገት ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡
ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆነችም ነው ያረጋገጠው።
ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ የእድገትና የዘመናዊነት መንገድ እንድትከተል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ለአብነትም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል፣ በአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን በማሳደግ፣ የሀገራዊ ምክክር ቅድመ-ዝግጅት በማገባደድና ማህበራዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች በጉልህ እንደሚታዩ አብራርቷል፡፡
እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያን “የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት” እንድትሆን እያስቻሉ ነው ሲል እውቅና ሰጥቷል፡፡
በቀጣይ ዓመታት ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን ወደ “አዲስና የላቀ ስኬት” መምራቱን እንደሚቀጥል ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለው ጥልቅ ትብብር አጽንኦት በመስጠትም የሁለቱ ፓርቲዎች መሪዎች ከዚህ ቀደም የደረሱባቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡
በቀጣይ የቻይናን እና የኢትዮጵያን ትብብር በሁሉም ዘርፎች በማስፋትና በማንኛውም ሁኔታ የማይናወጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ሆኖ የበለጠ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል።
ሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ የኢትዮጵያን ቀጣይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የሚቀርፅበት ወሳኝ ሁነት እንደሆነና ለሀገራዊ ልማት ወሳኝ የሆኑ ቀጣይ ግቦችን እንደሚቀመጡ እምነት እንዳለው አስታውቃል፡፡
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ለብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ስኬት መልካሙን ሁሉ መመኘቱንም የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡