በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ተጨማሪ 8 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጠ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ተጨማሪ ስምንት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።
መርማሪ ፖሊስ ባለፈው በተሰጠው 11 ቀን ያከናወናቸውን ተግባራት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል።
በዚህም የተጠርጣሪዎችንና የምስክሮችን ቃል መቀበል እንዲሁም በንብረት ላይ የደረሰብ ጉዳት የማጣራት ተግባራት ማከናወኑን ነው ያስረዳው።
ፖሊስ በተፈጠረው ሁከት በሶስት ተቋማት ብቻ ከ166 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን የሚገልጽ ማስረጃ ማግኘቱንም ገልጿል።
በቡራዩ በደረሰ ጉዳት የአራት ሰው ህይወት ማለፉንና አራት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ከዚህ ባለፈም 7 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ንብረት ወድሟልም ነው ያለው ለፍርድ ቤቱ፡፡
ከቡድኑ ከተገኙ ሰባት ሽጉጦች ውስጥ ሁለቱ የአቶ በቀለ ሲሆኑ ህገወጥ ናቸው ያለው መርማሪ ፖሊስ እስካሁን በእርሳቸው ላይ በአጠቃላይ 50 ምስክር ማዳመጡን ተናግሯል።
በተጨማሪም በ5 ክፍለ ከተሞችና በተለያዩ ተቋማት በአጠቃላይ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በማብራራት በአቶ በቀለ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ብሄርን ከብሄር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ማጋጨታቸውን የሚያመላክት የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ አለኝ ብላል።
ተጠርጣሪዎቹ ሁከት እንዲነሳ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ መልዕክት የተቀበሉ ሰዎች ያደረሱትን ጉዳት እያጣራ እንደሚገኝም አስረድቷል።
ቀሪ የምርመራ ስራዎች አሉኝ ያለው መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ምስክር መስማትና ሽጉጦችን ለፎረንሲክ ምርመራ ልኮ ውጤት እየጠበቀ እንደሚገኝ ጠቅሷል።
በንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በደብዳቤ ጠይቆ ከተቋማት ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን በመጥቀስም 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ቃል እንዳልተቀበላቸው ጠቅሰው የተጠረጠሩበት ወንጀል እኔን አይመለከትም ብለዋል።
በተጨማሪም አቶ በቀለ ሽጉጡ አንድ ጊዜ በቤታቸው በሌላ ጊዜ ደግሞ በመኪናቸው ተገኘ ያለው መርማሪ ፖሊስ በተመሳሳይ አስከሬኑን በማገት በሌላ በኩል ደግሞ አስከሬኑ እንዳያልፍ በስልክ ደውለው ማለቱ የተለያየ ሃሳብ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይህን ይገኝዘብልኝ ብለዋል፡፡
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አስቀድመው አስከሬኑ እንዳያልፍ መንገድ እንዲዘጋ በስልክ አዘዋል ብሎ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ሽጉጡ የእኔ አይደለም በሚለው መቃወሚያ ሁለቱ የእርሳቸው መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ክርክሩን የተከታተለው ፍርድቤቱ የአቶ በቀለ ልጆች ላፕቶፕ፣ ኮምዩተር እና መኪናቸው የወንጀል ፍሬ ካልሆነ ተጣርቶ አንዲመለስላቸውም በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
መርማሪ ፖሊስ ያቀረበው ተጨማሪ 14 ቀናት የሚወስድ የምርመራ ጊዜ የለም በማለትም ቀኑ ሊፈቀድ እንደማይገባ ተከራክረዋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆችም ደንበኛቸው የዋስ መብታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ የጅምላ ክስ የሚያቀርብ በመሆኑም ደንበኛቸውን ብቻ የሚመለከት ያቅርብ ሲሉም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
ተጠርጣሪውና ጠበቆቻቸው የመገናኛ ብዙሃን ውሳኔ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ ዘገባ እያቀረቡ በመሆኑ ትዕዛዝ ይሰጥልን ሲሉም ጠይቀዋል።
ጠበቆች ደንበኛቸውን ለማግኘት እንደተቸገሩ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አቶ በቀለ የተጠረጠሩበት ወንጀል ስፋት ያለው፣ ውስብስብና ሌሎች ግብረ አበሮች ያሉበት በመሆኑ የተጠርጣሪው ምርመራ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ሊለያይ እንደማይችል ገልጿል።
የምርመራ ስራውን በፍጥነት ለመጨረስ እየተሰራ ቢሆንም በየአካባቢው የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ጊዜ የሚወስድ መሆኑንም አስረድቷል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በሳምንት ሶስት ቀን ከደንበኛቸው ጋር እንዲገናኙ ፕሮግራም ቢወጣም ጠበቆች በተናጠል በመሄድ ፕሮግራሙን እያከበሩ እንዳልሆነ ገልጾ፤ በፕሮግራሙ መሰረት መስተናገድ ካልቻሉ ማጣራት አድርጎ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጧል።
ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተጨማሪ ስምንት ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪና ጠበቆች መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ላቀረቡት አቤቱታ መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው ያቀረቡትን ጉዳይ የሚመለከት ዝርዝር አቤቱታ ቀጠሮ ሳይጠብቁ እንዲያቀርቡና አቤቱታው አግባብ ሆኖ ከተገኘ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል።
በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩት እነ አራፋት አቡበከር እና እነ አዲሱ ቶሎሳ ላይ መርማሪ ፖሊስ ያደረገውን ማጣራት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።
ግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱም ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ