የኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክን ትብብር ለማጠናከር መስራት እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከቼክ ሪፐብሊክ የኢንዱስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ጄ ካቫሊሪክ ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በትናንትናው ዕለት በፕራግ በተካሄደው የኢትዮ-ቼክ ሪፐብሊክ የፖለቲካ ምክክር መድረክና የቢዝነስ ፎረም ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡
ከስብሰባው በኋላ በነበራቸው ቆይታም የሀገሪቱን የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ሚኒስትር ጨምሮ ከተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ አምባሳደር ምስጋኑ÷ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በውሃ እና ኢነርጂ ፣ በማምረቻ ዘርፍ እንዲሁም በመከላከያ ኢንዱስትሪ ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።
ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ሀገራቱ የተለዋወጡትን የጋራ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምስረታ ረቂቅ ሠነድ ባጭር ጊዜ ተፈራርመው ወደ ሥራ ለማስገባት አስፈላጊነት ላይ መስማማታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡