Fana: At a Speed of Life!

ከ11 ሚሊየን ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ዋለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት 11 ነጥብ 16 ሚሊየን ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ መዋሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የአፈር ሃብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሊሬ አቢዮ÷በግማሽ ዓመቱ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ማልማት መቻሉን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ ማሳ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማልማት መታቀዱን ጠቁመው÷ ዕቅዱን ለማሳካት የርጥበት ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአፈር ለምነትና ጤንነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት ማሣን ማልማት በሚኒስቴሩ ትኩረት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች ቀዳሚ መሆኑን አመልክተዋል።

ኮምፖስት፣ ቨርሚ ኮምፖስት እና ባዮስላሪ ኮምፖት የመሳሰሉ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን አርሶ አደሮች በማዘጋጀት ማሣቸውን እንዲያለሙ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትና የአጠቃቀም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው÷አርሶ አደሮች የባለሞያዎችን ምክረ ሃሳብ ተቀብለው እየተገበሩ መሆናቸው አበረታች ውጤት እንዲመዘገቡ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የተጎዳ አፈር ጤንነትንና ለምነትን ለመመለስ ያለውን ፋይዳ በመገንዘቡ የመጠቀም ፍላጎቱ እያደገ መምጣቱንም አስረድተዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.