Fana: At a Speed of Life!

ስዊድን ኢትዮጵያ የምታካሂደውን የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት እንደምትደግፍ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ስዊድን ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ውጤታማነት ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች፡፡

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር  ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር ) ከስዊድን አምባሳደር ሃንስ ኤነሪክ ሉንድከስት እና ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጋር በማህበራዊ ጥበቃና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ዓላማ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጉዳይ በተመለከተ ባሉ አዳዲስ የትብብር መስኮችና በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

በውይይቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)  መንግስት ለችግር ተጋላጭ ዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ የከተማና የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔትና ስራ ፕሮጀክት በመቅረፅ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እያጋጠመ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ÷ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ዜጎች በመኖራቸው ስድስተኛው የሴፍቲኔት ፕሮግራም ቀረፃ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዊድን መንግስት በስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅትና በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በኩል ላለፉት ስምንት ዓመታት በተለይ በኢትዮጵያ ያለውን የማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ ከማጠናከር አኳያ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን አንስተዋል።

የስዊዲን አምባሳደር ሃንስ ኤነሪክ ሉንድኩስት በበኩላቸው፥ ስዊድን በኢትዮጵያ በሰላም ግንባታ፣ ስራ ፈጠራ፣ ማህበራዊ ጥበቃ እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ ስታደርግ መቆየቷን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴሩ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ያለው የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ስዊድን ድጋፍ እንደምታደርግ አምባሳደሩ ማረጋገጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.