የእስራኤል ኢነርጂና መሰረተ ልማት ሚኒስትር የኢትዮጵያ ቆይታቸው የሃገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእስራኤል ኢነርጂና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ኢሊ ኮህን የኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱን ሀግራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ ከተለያዩ ሚኒስትሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ሁለቱን ሀገራት በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በጤናው ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፣ ከማዕድን ሚኒስትር ኢ/ር ሃብታሙ ተገኝ፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) እንዲሁም ከሌሎች ሚኒስትር ዴኤታዎች ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከሥራ ሀላፊዎች ጋር ሀገራቱ በፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርምር፣ ስታርትአፕ ልማትና በሃይል ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይም መምከራቸውን አንስተዋል፡፡
ውይይቱ የእስራኤል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በር የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶክተር አብርሃም ንጉሴ በበኩላቸው÷ የእስራኤል ኢነርጂ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር አሊ ኮህን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሁለቱን ሀገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከትናንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ ቡና መደነቃቸውን እና ቡና ወደ እስራኤል በስፋት በሚገባበት መንገድ ዙሪያ በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡
በፀጋዬ ንጉስ