የንግዱ ማህበረሰብ ገዥ ትርክትን ለማጎልበት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግዱ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከርና ገዥ ትርክትን ለማጎልበት ወሳኝ ሚና እንዳለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
ለኢትዮጵያ ዘላቂ የሰላም ግንባታ የግሉ ዘርፍ ሚና ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።
በመድረኩ “የጋራ ትርክት ግንባታና ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ የግሉ ዘርፍ ሚና” በሚል የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት÷ የጋራ ትርክት መገንባት ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጋራ ትርክት በመገንባት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ አኳያ የንግዱ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን የህብረ ብሔራዊ አንድነትና ገዥ ትርክትን ለማጎልበት ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ያብራሩት፡፡
የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው÷በህዝቦች መካከል ግንኙነትን ለማዳበርና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ንግድ ዓይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፥ ይህንንም ይበልጥ ማስቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ እያከናወነ ባለው ዘርፈ ብዙ ተግባራት የግሉ ዘርፍ ያለውን ዓይነተኛ ሚና ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተለይም ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ከማድረግ በተጨማሪ የግጭቶች መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ ለመከላከልና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡