የሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እና የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የችግኝ ተከላ አካሄዱ
አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 21 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እና የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ÷ወጣቱ ትውልድ አረንጓዴ የሆነች የነገይቱን ኢትዮጵያ ለማየት ችግኝ የመትከል ባህልን ሊያዳብር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት ዛሬ በሱማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ በሚገኘው አየር ደጋ ጤና ጣቢያ በመገኘት ከከተማው ወጣቶች ጋር በመሆን ችግኝ በተከሉበት ወቅት ነው።
በሱማሌ ችግኝ የመትከል ባህሉ ዝቅተኛ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ወጣቱ ትውልድ ይህን ባህል እንዲያዳብር ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።
ተፈጥሮን መንከባከብ ዜጎችን ከድህነት የሚያወጣ ነው ከተደጋጋሚ ድርቅ የሚከላከል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
በአካባቢ መራቆት በሚመጣው ችግር ይበለጥ ተጋላጭ የሆኑት ደግሞ ሴቶች እናቶችና ህፃናት በመሆናቸው ሴቶች የችግኝ ተከላ ልምድን እንዲያዳብሩም መሰራት እንዳለበት ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ተናግረዋል።
የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን በዛሬዉ እለት በለገጣፎ ከተማ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር አካሂዷል ፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች÷ ከሄሎ ታክሲ እና ከኦክሎክ ሞተርስ ጋር በመሆን 2ሺ ችግኞችን ነዉ በከተማዋ የተከሉት፡፡
በችግኝ ተከላዉ ላይ የተሳተፉት የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት ÷መስሪያ ቤታቸዉ ለቱሪስት መዳረሻ በሆኑ አከባቢዎች በተያዘዉ ክረምት የችግኝ ተከላ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዉ ፣በለገጣፎ ከተማም የተደረገዉ የዚሁ አንድ አካል ነዉ ብለዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ከግል ድርጅቶች ጋር በመሆን በዛሬዉ እለት 2ሺ ችግኞች መተከላቸዉን ተናግሯል፡፡
በአጠቃላይ በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ደረጃ ለአረንጓዴ አሻራ ፣የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ አካባቢዎች 26ሺ ችግኝ ለመትከል እቅድ ከተያዘዉ ዉስጥ 10 ሺህ 300 የሚሆነዉን እስካሁን መትከል ተችሏልም ነው ያሉት ።
በብስራት መለሰ እና ማህሌት ተክለ ብርሃን
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።