Fana: At a Speed of Life!

ለአፍሪካ ህብረት ጉባዔ እንግዶች ቀልጣፋ የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎ ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 217 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለሚመጡ እንግዶች ቀልጣፋ የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎቶችን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ኢትዮ- ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቁ።

38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን ፥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።

የኢትዮ-ቴሎኮም ቺፍ ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር መሳይ ውብሽት ፥ እንግዶች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከመድረሳቸው ጀምሮ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በሚያርፉባቸው ሆቴሎችና በህብረቱ ዋና መስሪያ ቤትም የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በማቋቋም የሲም ካርድና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በቀላሉ የሚያገኙበት ሥርዓት ከወዲሁ መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በጉባዔው ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በቆይታቸው ከኔትወርክ ጋር የተያያዘ የቴክኒክ ችግር እንዳያጋጥማቸው በቂ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

ለዚህም አስተማማኝ የ4 ጂ እና 5 ጂ ኔትወርክ በጥራት እንዲያገኙ በዋና ዋና ማዕከላት ማሻሻያ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የአገልግሎት መቋረጥ እንዳይፈጠር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ የባለሙያ ስምሪት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ዲቪዥን መርቻንትና ኤጀንት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ብሌን ኃይለ ሚካኤል በበኩላቸው ፥ እንግዶች የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሬ እንዲፈጽሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሆቴሎችም የፖስ እና ሌሎች የዲጂታል ባንኪንግ አማራጮችን በመጠቀም ግብይትና ክፍያ የሚፈጽሙበት ዕድል መፈጠሩን ማንሳታቸው የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.