Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

 

ብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ መስኮች የተገኙ ውጤቶችን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

 

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ፓርቲው ባሳለፋቸው ውሳኔዎች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።

 

ለስኬታማነቱም የጋራ ገዥ ትርክትና ሀገራዊ ሥነ ልቦናን ይበልጥ ማዳበር ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

ለአብነትም ለውጡን ተከትሎ ለበርካታ ችግሮች መንስኤ የሆነውን ነጠላ ትርክት በሀገራዊ አሰባሳቢ ትርክት ለማረም መሰራቱንም አንስተዋል።

 

ፖለቲካው ከነበረበት ጽንፍ ተላቆ የመሃል ፖለቲካ እሳቤ ቦታ እንዲይዝ መደረጉ ለብሄራዊ መግባባት መሰረት መጣሉን ጠቁመው፤ በዚህም ውጤት መምጣቱን በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ መገምገሙን አክለዋል።

 

በቀጣይም በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ ገቢራዊ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

 

ሀገራዊ መግባባቱ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባትን በማለሙ ለውጤታማነቱ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

 

በጋራ ትርክቱ መሰረታዊ ተቃርኖዎች ተፈትተው ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

 

በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መሥራት አለብን ያሉት ሚኒስትሩ ህዝቡ፣ ፖለቲከኞች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ዳያስፖራውና ሊሎችም በትጋት መሳተፍ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.