ጠንካራና የማይበገር የጤና ስርዓት ለመዘርጋት በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል- ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ጠንካራና የማይበገር የጤና ስርዓት ለመዘርጋት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በቁርጠኝነት ትሰራለች ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
ኢትዮዽያ አባል የሆነችበት የዓለም ጤና ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ 156ኛው ስብሰባ በስዊዝርላንድ ጀኔቫ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ÷ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጤና ክብካቤን በማጎልበትና ጠንካራ የጤና ስርዓት እንዲኖር በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
ሚኒስትሯ ለዘላቂ የጤና መሰረት ስርአት፣ የሀገር ዉስጥ የህክምና ግብዓት ምርትን ለማሳደግ ፣ ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎትን ለማሟላት እና ብቁ የጤና ክብካቤ ሰራተኛን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።
የአለም ጤና ድርጅትና ሌሎች አጋር አካላትም ጥራቱ የተጠበቀ፣ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የተያዘዉ ግብ እንዲሳካ ዘርፈ ብዙ ድጋፋቸዉን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
መድረኩ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ተሳትፎና ተቀባይነት በማጠናከር በጤና ዲፕሎማሲ ረገድ ከፍተኛ ሚና ለመጫወት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ወቅታዊ የሆኑ የዓለም አቀፍ ጤና አጀንዳዎች ላይ ለዓለም ጤና ጉባኤው የውሳኔ ምክረ ሃሳቦች እንደሚያቀርብም ይጠበቃል መባሉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡