የግል ተቋማት አሰሪዎች ሰራተኞቻቸውን ከኮቪድ-19 ለመጠበቅ የሚያደርጉት ድጋፍ ቀንሷል-ኢሰማኮ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የግል ተቋማት አሰሪዎች ቸልተኝነት እየታየባቸው መሆኑን የኢትዮዽያ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
የኢትዮዽያ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ÷የግል ተቋማት አሰሪዎችም ሆነ ሰራተኞች ስለኮሮና ቫይረስ አደገኝነት የክልል ኤፍኤሞች ጨምሮ በተለያዩ የሚድያ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ሆኖም በግል ተቋማትም ሆነ በሰራተኞች ዘንድ የቸልተኝነትና የጥንቃቄ ጉድለት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።
ችግሩ እየተባባሰ ሲመጣ በሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትር ወደ ሚመራው የሶስትዮሽ የስራ ቦታ ፕሮቶኮል ኮሚቴ ከሰራተኞች ለቀረበው ቅሬታ በማስማማት በርካታ ችግሮች የተፈቱ ቢሆንም በሁሉም ቦታ ግን ተደራሽ አይደለም ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን ህጉን አክብረው ለሰራተኞቻቸው የንፅህና መጠበቅያ የሚያቀርቡ ተቋማትና ርቀታቸውን ጠብቀው የሚያሰሩ እንዳሉ ገልፀው÷ አንዳንድ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ተቋማት ግን ህጉን ቸል በማለትና ለሰራተኞቻቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው ለቫይረሱ እንዲጋለጡ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡
በምሳሌነትም አንድ ስሙን መጥቀስ ያልፈለጉት የውጭ አገር የግል ተቋም ለሰራተኞቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ባለመደረጉ በርካታ ሰራተኞች በቫይረሱ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
ቫይረሱ በሀገራችን ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ ውሃና የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና ለሰራተኞች ሲያቀርቡ የነበሩ ድርጅቶችም የቫይረሱ ስርጭት ከፍ ባለበት በአሁኑ ወቅት ቸልተኝነት እየተስተዋለ ይገኛል ብለዋል።
የሚመለከተው አካል ለድጋፍና ክትትል ወደ ተቋማት ሲሰማራ ለታይታ የሚቀመጡ የንፅህና መጠበቂያዎች በሌላው ጊዜ እንደማይቀርቡ ከሰራተኞቹ ለማወቅ መቻሉም ነው የጠቆሙት፡፡
ሰራተኞች በግል አሰሪዎቻቸው ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቀደም ብሎ በወጣው የሶስትዮሽ የስራ ፕሮቶኮል መሰረት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጋር በመሆን የማስማማትና የማስተካከል ስራዎች መሰራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በስምምነት መቋጨት ያልቻሉ ቅሬታዎች በየወረዳው ወደ ተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀምያ ማእከላት ቢላክም ተገቢውን ምላሽ እየተሰጠው አይደለም ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ሰው በጤናና በህይወት ሲኖር ነው ሃብት ማፍራትም ሆነ ማደግ የሚችለውና አሰሪዎች ከጥንቃቄ ጉድለት ሰራተኞቻቸው ሊጎበኝ የሚችለው ኮቪድ-19 ለእነሱም እንደሚተርፍ በመገንዘብ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።