የአማራ ክልል ምክር ቤት ከ62 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የክልሉ መንግስት በጀትን አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ከ62 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የአማራ ክልል መንግስት በጀትን አፀደቀ።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ቀጥሎ ባካሄደው በመደኛ ስብሰባውም የ2013 የክልሉ መንግስት ረቂቅ በጀትን ተመልክቷል።
በዚህም የአማራ ክልል ምክር ቤት 62 ቢሊየን 698 ሚሊየን 672 ሺህ 937 ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2013 የአማራ ክልል መንግስት በጀት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አጽድቆታል።
ከአጠቃላይ በጀቱ 24 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ከክልሉ የሚሰበሰብ፣ 38 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ከፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እና 0 ነጥብ 2 ቢሊየን ብሩ ከውጭ ዕርዳታ የሚገኝ ነው።
የፌደራል መንግሥት የሰጠው በጀት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ23 ከመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፥ የ2013 በጀት ከ2012 በጀት ጋር ሲነጻጸር በ15 ነጥብ 3 ቢሊዮን (32 ነጥብ 4 ከመቶ) ጭማሪ አለው።
በጀቱ በአብዛኛው ተጀምረው ያላለቁ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ትኩር የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።
እንዲሁም በበጀቱ የድህነት ቅነሳ ተኮር የሆኑ የልማት ስራዎችን ማከናወን ቅድሚያ የተሰጠው መሆኑም ነው በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባዔ ላይ የተነሳው።
በ2013 በጀት ዓመት የውጥ ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት የሚሰራበት መሆኑም ነው የተገለፀው።
በተጨማሪም የአማራ ክልል ምክር ቤት የ2012 በጀት ዓመት 3 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀትን ከተመለከተ በኋላም አጽድቋል።
በለይኩን ዓለም
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።