ዩኒዶ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዓለም አቀፍ አጋርነት እና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ፋቱ ሀይዳር ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት ÷ አምባሳደር ምስጋኑ በብሔራዊ የኢንዱስትሪ ልማት እየተተገበሩ በሚገኙ ፕሮጀክቶች ማለትም በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በግብርናና ምግብ ማቀነባበሪያ ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።
ለዚህ ሥራ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ እና ዩኒዶ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በአቅም ግንባታ፣ በልምድ እና በቴክኖሎጂ ልውውጥ ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር ተደርጓል።
ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ፋቱ ሀይዳር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከወራት በፊት የተካሄደውን ከረሃብ ነጻ ዓለም ኮንፈረንስ በተሳካ መንገድ በማስተናገዷ አመስግነው ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።