በጉባዔው ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትና የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮዋን ለሌሎች ሀገራት አካፍላለች – አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርትና በአረንጓዴ አሻራ ያስመዘገበችውን ውጤት ለሌሎች ሀገራት በተሞክሮነት ማካፈሏን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋሁን ጎበዛይ በሰጡት መግለጫ÷ በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ከተገኙ ስኬቶች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያን ስኬትና አዲስ ገጽታ ለዓለም ማሳወቅ ነው ብለዋል፡፡
በግብርና ዘርፍ በተለይም በስንዴ ምርት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ስኬት ለሌሎች ሀገራት በተለያዩ መንገዶች በተሞክሮነት ማካፈሏን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው ባደረጉት ንግግር በስንዴ ምርት እና በአረንጓዴ አሻራ የተገኙ ጉልህ እምርታዎችን ለታዳሚዎች ማስረዳታቸውን አንስተዋል፡፡
በጉባዔው በተደረጉ የጎንዮሽ ውይይቶችም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከር መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ጉባዔውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦች በማስተዋወቅ ረገድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ነው ያነሱት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ከህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ የበለጡ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በትኬት ማስተናገድ የሚያስችል ዝግጁነት እንዳለው ማሳየቱንም ሚኒስትር ዴዔታው ተናግረዋል፡፡
ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የህብረቱን የመሪዎች ጉባዔ ተሳታፊዎች የሚመጥን የላቀ አገልግሎት መስጠታቸውንም አብራርተዋል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪዎች ጉባዔው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት ባህልን ባከበረ መልኩ እንግዶች ቆይታቸው የሰመረ እንዲሆን ለሰጡት መስተንግዶ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ